Tuesday, April 16, 2013

ሰላም ላንተ


ሰላም ላንተ ይሁን ከእናትህ ጉያ ወጥተህ እዳሪ መሬቷን ሳታርስላት ፣ አባትህ አቅሙ በደከመ ጊዜ ሳታግዘው ለተለየሃቸው፣ ምሽትህ ምሰሶዋ ሆነህ ሳትጠግብህ በስስት ለራቅካት ልጆችህ ቤት ሲገቡ ሞገሳቸውን አንተን ላጡ ላንተ ሰላም ላንተ ለወታደር ፤ ወጥቶአደር ሁሌም ድንበር ሉዐላዊነታችንን የምትጠብቅ የያዝነውን የማታስነጥቅ ከጥንት እስካን በተወራረሰ የደም እና የወኔ ውርስ የታተምክና የተሰራህ ለእኛ ሰላምና ለበላዮችህ ሰላምታ ስትሰጥ ስትደክም ለምትኖር ላንተ፤
ሰላም ላንተ ጦርነት ካልመጣና የሹመኞችህ ወንበር ካተነቀነቀ በቀር ትውስታ ውስጥ ለማትገባው፣ በየጊዜው በግምገማ ግራ ለምትጋባው፣ እኛ ለመኖር ስንታትር አንተ ለመሞት የቆረጥከው ላንተ፤
ለሹመኞቹ ሰላምታችን ሁሉ ባንተ ተጠቃሎ ስለሚደርስልን መጥቀስ አያስፈልገንም ነገር ግን ከልብ የመነጨ ኩራታችንን እሳቱ ላይ ለምትጣደው የአዳምና የሔዋን ዘር እናቀርባለን፡፡
በዚህ ሰሞን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መከላከያ ሠራዊት ቀን ወይንም ሳምንት እየተከበረ ነው እናም ግራ የሚያጋባ ስሜት ተሰማኝ ምክንያቱም ኢትዮጵያ እስካሁን የቆየችው ከላይ የተጠቀሰውን ስም ባነገበው ሠራዊት እና በእነ ጄኔራል ፣ ኮሎኔል ወዘተ ብቻ አይደለም ገና እነ ፊታውራሪ ደጃዝማች ግራዝማች እያሉ ጀምሮ ከሩቅ ሆኖ በሚተኮስበት ወቅት ሳይሆን መሣሪያ እስከ አፍንጫቸው በታጠቁ ዘመንኛ ሠራዊት በጦርና በጎራዴ ገጥሞ ሀገር ድንበር ርስት ባስጠበቀውም ጭምር ነው እንጂ በመሐልም የመርዝ ጋዝ እየዘነበበት እንዲሁም ከጎረቤትም ለመናገሻ ከተማዋ አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት እስኪከትሙ ድረስ ሀገር መሬት ውስጥ ገብተው የወረሩንንን በመመከት ነው እናም አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት በዓል ቢሆን እመኝ ነበር ግን የአሁንና የአሁን ብቻ መሆኑ አሳዝኖኛል፡፡
ታሪኮቹም ሁሉ የሚወሩት የሚወሱት ሁሉ በጣም በሚገርም ሁኔታ የአሥራ ስምንትና የሃያ አመት ታሪክ ነው፡፡ ለምን የቅርብ ታሪክ ቀረበ የሚል ሀሳብ የለኝም ግን ሁሉም ነገር የሚነሳው ስለ ‘ለውጡ’ ትውልድ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ለውጡ ተሳክቷል ወይስ ጠፍቷል የሚለው ተጨማሪ ክርክር ቢፈጥርም ማለቴ ነው፡፡ ይሄ ግን በምንም መለኪያ ትክክል ሊሆን አይችልም ፡፡ ነባሩም ፣ የተገለለውም ፣ ያለውም ፣ ያለፈውም መታወስ አለበት ምክንያቱም የኢትዮጵያ ታሪክ በሺዎች እንጂ በአሥራዎች የሚቆጠር ስላልሆነ፡፡ እናም ከምንም ነገር ተነስተን የሃያ ዓመታት ታሪክን እንደ ሙሉ ታሪካችን ደጋግመን በጆሯችን ስንሰማ ከባድ ቅሬታ እየተሰማን ነው፡፡
በነገራችን ላይ የሃያውም ዓመታት ታሪኮች እንዳሉ የአንድ ብሔርን ማንነት እና ልፋት ልዕልና ብቻ የሚያሳይ ነው፡፡ እውነት ግን ሌሎቹ አልታገሉም ? ታለዋል እንጂ ያውም የታገሉትም ገዢው ፓርቲ እንደሚለው አንዳንድ ጥቅመኞችን ሰብሰብ አድርገው ይሄኛውም ታግሏል ብለው የነሱ ሎሌዎች በማድረግ እጆቻቸውን ለማስረዘም በተደረገው ሴራ ሴራ ዓይነት ዓይደለም ፡፡ ደግሞስ ቆይ እነ ኢህአፓ ፣ ኢዲዩ የመሳሰሉት ለሀገር መስሎኝ የታገሉት እንጂ ለነጮች ተሸጠው ወይም ሀገራቸውን ለማስረከብ አይደለም እንደኔ እንደኔ፡፡ ቀድመዋል ለመጀመርም ቢሆን ነገር ግን በአንዳንድ ምክንያቶች ከሜዳው ተገለዋል አንዳንዱም ታፔላውን ቀይሮ ወደዚህ ተጠምዝዟል፡፡ እነጋሼ ከመጀመሪያውም አንድ ሀገር ብለው አልተነሱም አሁንም አያስቡም ስለተመቻቸው ነው ቦታውን ያደላደሉት፡፡ ነገር ግን  የኢትዮጵያ ህዳሴ መንገድ ፈር ቀዳጅ ሆነው አረፉት፡፡ የታሪክ ንጥቂያ ከባድ ነው፡፡ ያውም ለመበታተን የተነሳ ኃይል አሁን ደግሞ የአንድነት ሰባኪ እንዴት ይሆናል፡፡
ይሁን ምናልባትም በሕይወት ተምሯል ተብሎ ሲታለፍ ፡፡ የሚናገረው የሚሰራው ነገር ሁሉ ተምታቷል፡፡ ሕብረ ብሄራዊነትን ያነገበ የመከላከያ ሠራዊት ተብሎ ይለፈፋል፡፡ ነገር ግን እሳቱ ላይ የሚጠበሱት ሠራዊቶች ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ከሌሎች ክልሎች የተውጣጡ ይሆኑና ወይ ለግምገማና ወሬ ለማቀበል ታማኝ ስለሆኑ ብቻ አብረዋቸው የሚሆኑ ካልሆኑ በስተቀር ሁሉም አመራር ላይ ያሉት የአንድ ብሔር አባላት ናቸው ለነገሩ የተነሳንበት ጉዳይ እንደነሱ አጠራር ‘የፌደራል መከላከያ ሰራዊት ቀንን’ በማስመልከት ስለሆነ ነው እንጂ ሁሉም ቦታ እነሱ ብቻ ናቸው፡፡ ልክ እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ሲነሳ ኢነተርሃምዌይ ይሉናል፡፡ ነገር ግን እራስን ከሌሎች ነጥሎ የጥቅም አደላዳይ እና ብቸኛ ተጠቃሚ ከመሆን የበለጠ ኢንተርሃምዌይነት አለ እንዴ? በጥያቄ ይደር፡፡
ይህ እንዳለ ይቆይና ስለ አውደ ርዕዩ ትንሽ ልበል፡፡ ጉብኝቱ መልካም ነበር ግን ብዙ የጠበቅነው ነገር አልሆነም ወታደራዊ ሰልፎች፣ ፓራኮማንዶ ትርዒት፣ ተሻሻሉ የተባሉትም መሣሪያዎች በዛ ብለው ቴክኖሎጂዎቹም በተቻለ የመገጣጠም ሥራ ሳይሆን ከአንድ ምርት ቢያንስ አንዱን ክፍል እዚሁ ለማምረት ጥረት ቢደረግ፡፡ ሌላው ደግሞ ብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ሲቋቋም የግሉ ዘርፍ ሊደፍረው የማይችለውን የኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማንሳት ለማጠንከርና ለማበርታት ነው የሚል ነበር ግን አሁን ተራ የሚባሉ የፕላስቲክ /ተራነታቸው ሌሎች የግል ድርጅቶች የገቡበት ንግድ ስለሆነ/ ኤሌክትክ ሽቦ እና የመሳሰሉትን እናመርታለን ሲሉ ቅር ብሎኛል፡፡ እንዲሁም አንዳንዶቹ በቅርበትም የማውቃቸው ምርቶቻቸው ውጤታማ አልበሩም እነሱን ውጤታማ እንደሆኑ አድርጎ የማቅረብ የመሳሰሉት ነገሮችና ሌሎችም መታረም አለባቸው፡፡ ነገር ግን ለቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያደርገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን በዓለም ላይ እንደ መርህ የምንጠቀምባቸው ጽንሰሀሳቦች አብዛኛው የተገኙት ከወታደራዊ ሳይንስ ጠበብቶች ነው፡፡
እንደማጠቃለያ መቼም ቢሆን ደምና አጥንት ለከፈሉ አባቶቼና እናቶቼ እህት ወንድሞቼ አመራርም ሆናችሁ የበታች ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡ ለገዚው ፓርቲም ቆም ብላችሁ አስተውሉ ሁልጊዜም ምርጫ 97 መጥቶ አሁን ነው የገባን እያላችሁ አትሸውዱን ጊዜ ሰጥቶ ህዝብ አዳምጡን ሲላችሁ አንደበታችሁን ቆጠብ አድርጋችሁ ጆሯችሁን ዘርጋ አድርጉት፡፡ ብዙ ትምህርት ይገኛል አይዟችሁ አትናቁት፡፡ ምናልባት መሳሪያ አልታጠቀ ሊሆን ይችላል ግን ቀን ይፈታዋል የናንተን መሣሪያ፡፡ ልብ በሉ ሁሉንም አድራጎታችሁን ሕብረ ብሔራዊ አድርጉት የጎጠኝነት ፖለቲካችሁ እዛው ጫካው መልሱት ፡፡ ወይንም እናንተ ጫካ ተመለሱና …….

No comments:

Post a Comment