Sunday, February 3, 2013

የዘመኑ ሽለላ


መቼም አንባቢዎቼ ሁሉ ምን ዓይነት ዘመንኛ ሽለላ ተገኘ ሊሉ ይችላሉ፤ ቢሆንም ደግሞ አልፈርድባቸውም፡፡ ምክንያቱም አሁን አሁን ዘመናዊ ነገር ዘመናዊ ፈጠራ እየተባለ ከማዳነቅ ውጪ ድሮ የነበርንበትን አይተን መነሳት ተስኖናል፡፡ ከባዶ /ዜሮ/ ወለል ላይ እየተነሳን ሩቁ እየራቀን ሁሌም ማንነትን ማንቋሸሽ ሆኗል ሥራችን፡፡ ምናልባትም አባቶቻችን በደረሱበት ደረጃ ላይ ብቻ እንኳን ተነስተን ብንጀምር እራሳችንን ዓለም አሁን ያለበት ቦታ ላይ ነው የምናገኘው፡፡

የጽሁፌ መነሻ ሐሳብ ይሄ አይደለም ለነገሩ ግን ሁሌም የነበርንበትን ማስታወስ መልካም ነው በሚል ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ፉከራው ሽለላው ሁሉ ገንዘብ ከማግገኘት ጋር በጣም የተቆራኘ በመሆኑ ስልምንነጋገርባቸው ቁሶችም ሆነ ቅርሶች ማኅበራዊም ሆነ ባህላዊ እንዲሁም መንፈሳዊ ፋይዳ ማሰብ ተስኖናል፡፡ ወይም ላለማሰብ እራሳችንን አዘጋጅተናል፡፡
በሀገራችን ብቸኛውም አንጋፋውም የመንግስትም የፓርቲም የቴሌቪዥን ጣቢያ በዚህ መልኩ የተካነ ነው፡፡ በሥሩ ያሉ ሠራተኞችም እንደ ድርጅታቸው መካን ግድ ይላቸዋል፡፡ እዚህ ላይ አንባቢ ልብ ሊልልኝ የምፈልገው ነገር ግድ ይላቸዋል እንጂ ናቸው አላልኩኝም ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ እፍንፍን አድርገው መናገሪያ መስመር ያበጁልሃል እናም ከዚያ በላይ መሻገር የቴሌቪዥን ጣቢያውን ፖሊሲ መንካት ቀይ መስመር ማለፍ ነው እናም የተሰጣቸውን ክበብ ይዘው እንደ ዘይት ጨማቂ ግመል ይዞራሉ ነገም አሁንም ትላንትም አንድ ዓይነት ዘገባ አንድ ዓይነት ድርጅት ፡፡

በተለይ አንባቢዎቼ የመንግስት ወይም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ከሆነ ወይም መረጃው ካላቸው በጣም ይረዱኝ ይሆናል፡፡ ሚኒስትሩ አሉ ከተባለ የማይፈጸም የማይወርድ ትዕዛዝ የለም የትኛውም ሚኒሰቴር እንደሆነ የማረጋገጫ ጊዜ እንኳን የለም በለው ነው፡፡

ማንኛውም ዓይነት ስብሰባ ሲዘጋጅ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተብሎ ከስብሰባው አጀንዳ ቀድሞም ቢሆን ቢነሳ አይገርምም፡፡የውጪ ሀገር ዘፋኞችም ሲመጡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለሀገሪቱ የሚሰጠውን ዓለም አቀፍ ሽፋን በተመለከተ ሰፊ ዘገባ ቢቀርብም እንዲሁ፡፡ ነገርግን አንድ ባሕላዊ ስነስርዓት ወይም ኃይማኖታዊ በዓልን ድምቀት ለመስጠትም ሆነ የቱሪዝም ገበያ ለማግኘት ያለውን ጥቅምና ትርጉም ወደኋላ ማለት ከስህተትም እንደአባቶቻችን አባባል ነውር ነው፡፡ ወደኋላ አላልንም እንደሚሆን ማስተባበያው እጠብቃለሁ፡፡ እንግዲህ አሁን አሁን በጣም ሲበዛ እያየሁት እያስተዋልኩት የመጣሁትና ከጊዜ ወደጊዜ እየባሰበት የመጣ ነገር ቢኖር ይሄ በመሆኑ ነው ስለዚህም ልጽፍ የተነሳሁት፡፡ ይህንን ሀሳብ ስጽፍ በጉራጌ ዞን አንድ አካባቢ ከዋሻ ውስጥ ተቆፍረው የወጡ ኃይማኖታዊ ቅርሶችን የሚያሳይ ዘገባ እየቀረበ ነበር፡፡ መቅረቡ ባልከፋ /የዘገባ ሽፋን ሊባልነው እንግዲህ/ ግን ከተገኘው የመንፈሳዊ ሀብትነት አንድም ነገር ሳይባል /የሕዝቡ ነኝ በሚል ጣቢያ/ ስለ ቱሪዝም ሀብትነቱና ስለገቢ ማመንጫነቱ ሲነገር ስሰማ ገረመኝ ይህንን የተናገሩት አንድ ካህን ናቸው ግን ይህ ምላሽ ለተሰጣቸው ጥያቄ መሆኑ አያጠያይቅም ሌላው ደግሞ የፈለጉትን ሀሳብ ብቻ ቆርጠው እንዳቀረቡት ምንም ጥያቄ የለውም ለማን ነው ሌላው ጥያቄ የተጠየቀው ለእኛ ለህዝቡ አይደለም እንዴ፡፡ በነገራችን ላይ ከዚህ በፊት የሰማሁት ቢሆንም በታሪክነቱ ተቆፍረው ከወጡት ቅርሶች ውስጥ አንዱ ጥንት አባቶቻችን ዘመንኛው ብዕር ሳይሰራ በፊት ቀለም በውስጡ ተንቆርቁሮ መጻፍ የሚያስችል ብዕር ነበረበት አባቶቻችን በጣም ጠቢብ ነበሩ ልብ በሉ ጠባብ አላልኩም፡፡

ይሄም ይቅር በክልል ቴሌቪዥን የቀረበ ዝግጅት ነው ብለው ይለፉት በደቡብ ክልል ቴሌቪዥን ስለቀረበ፡፡ ነገር ግን የመስቀልን ደመራና የጥቀትን በዓል ማክበር መጀመሪያ መንፈሳዊ ዋጋው ተከፍሎት በትርፉ የቱሪዝም ትርፍ ቢያገኙበት ይሻላል፡፡ መቼም ሽልማት በዚህ ዘመን በምን እንደሚሰጥ ግራ ያጋባል ብቻ ግን ሆነም ቀረም ከተሸለሙት ጋዜጠኞቹ መካከል ጥምቀት እንደካርኒቫል ዓይነት ነው ብለው የሚናገሩም አልጠፉም፡፡ እንደው እውነት እንነጋገር ከተባለ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ራቁት ዳንስ የሚደነስበትን ስነስርዓት ከመንፈሳዊ በዓል ጋር ማነጻጸር አማርኛ ማወቅ ነው ወይስ ….. ምናልባት በባሕላችን ከሚዘወተሩት አባባሎች ውስጥ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እና የተያያዙት ነው የሚያስታቸው እንዳይባል የሚሸለም ሰው አጣርቶ እና አጥንቶ ነው የሚናገረው፡፡ ይህ ከላይ የጠጠቀሰው አባባል አንደኛ ታቦት ስለሚወጣ ስለታቦቱ ክብር ሁለተኛ ሰው ግልብጥ ብሎ ስለሚወጣ ትዳር ከእግዚአብሔት ነው የሚገኘውና ለሕይወት አጋርነት ለመምረጥ እንዲሁም ጥምቀት የመታደስ በዓል ስለሆነ ተያይዞ የሚመጣ ነው እንጂ እንደተባለው ዓይነት መነጻጸሪያ የሚገባው አይደለም፡፡

ሁልጊዜም ዘገባው በድምቀት ተከበረ ከተባለ በኋላ ሀገሪቱ ከቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ ያሳድጋል ይባላል፡፡ በቃ፡፡ እንደኔ እንደኔ ግን ብዙ ሊባልለት የሚችለውን በዓል አከባበራችንን ከሚባልለት ቀንሰን መንፈሳዊና ባሕላዊ ዋጋውን በመቀነስ ለቁሳዊ ጥቅም ማዋል ስህተት ነው፡፡ ይልቅ ዓይናችንን የሚያሳምሙንን ጆሮአችንን የሚያደነቁሩንን በይዘታቸውም ሆነ በቅንብራቸው የማይመጥኑ ዘፈኖችን አጣርተው እዲያቀርቡ ዝግጅቶቻቸውን እንዲፈትሹ /ባያደርጉትም ብሄራዊ ግዴታችን ነው ለበለጠ ለውጥ አስተያየት መሰጣጠት/ አሳስባለሁ፡፡ ካልሆነ ግን ዝግጅቱ መስጦን ሳይሆነ ስለሀገራችን ሁኔታ ማየት ማዳመጥ የምንፈልግ ዜጎችን እያሰላቻችሁ ነውና እባካችሁ እላለሁ፡፡