Wednesday, March 21, 2012

በማንኛውም ነገር እንማር


በሕይወታችን ሁልጊዜም አንድ ዓይነት መልስና መንገድ ብቻ ያለ የሚመስለን ሰዎች በብዛት ተሳስተናል ፡፡ ነገር ግን ብዙ ማስተዋል ያለብን ነገር አለ ፡፡ ወደዚህ ምድር ስንመጣ ያለምክንያት እንዳልመጣን ሁሉ ስንኖርም በዙሪያችን የሚያጋጥሙን ነገሮች ሁሉ ያለምክንያት አይደለም፡፡ 
በነገራችን ላይ እኔ ይሄንን ጡመራ ስጀምርም ብዙ ጊዜ ሀሳቤን እንድገልጽባቸው የምፈልጋቸውና ሳስተውላቸው መታረም ይገባቸዋል ብዬ የማስባቸውን ጉዳዮች በግልጽ መናገር እና መጻፍ እፈልግ ነበር ግን ተናጋሪ ብቻ ለመሆን አይደለም በተቻለ አንባቢም ለመሆን ነው ፡፡ ስለዚህም ከዚህ በኋላ የምጽፋቸው ጽሁፎች ሁሉ የሚያጠነጥኑበት መንገድ ሁሉ በሀገር ጉዳይና
በአጠቃላይ የሕብረተሰባችን ሁለንተናዊ ዕይታዎች ላይ ይሆናል ፡፡
ስለዚህም በመግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት ሀገር የምትመራው በፖለቲከኛ ብቻ አይደለም፡፡ ዕድገት የሚመጣው በመንግስት ብቻ አይደለም፡፡ ሕዝብም ሁልጊዜ ጠያቂ እና ጣት ጠቋሚ አይደለም፡፡ መንግስትም ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ብለው ያሰቡት ብቻ ውጤታማ ነው ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህም ከሕዝቡ በተለያዩ መስኮች የሚመጡ ግብዓቶችን በአስተዋይነት መንገድ መከታተልና ማዳመጥ፡፡ ሕዝብም የሚደረገው ሁሉ እርኩስ ነው ሁሉም ቅዱስ ነው ብሎ ከማመስገንና ከማማረር የጭፍን አካሄድ መላቀቅ አለብን፡፡
የምናስበውና የምንነጋገረው ሁሉ ለሀገራችን የነገ ተስፋ እና ዕድል ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ የጠበበ ዕይታዎቻችንን ቀን በቀን በማስተካከል እና ለማዳመጥ በመዘጋጀት መስተካከል አለብን ፡፡ ልጆቻችን ወደየት እየሄዱ ነው ሳይሆን ጥያቄው ምን ዓይነት ስነምግባር መገብናቸው ፣ ምን ያህል ዕድል ሰጠናቸው ፣ ምንያህል እኛስ ለመቀበል መሠረታዊ ዝግጁነት አለን የሚለው መመለስ አለበት፡፡ ምክንያታዊ የሆነ ነቀፋ እና ድጋፍ ለማድረግ እራስን ከዛሬ ጀምሮ ማዘጋጀት አለብን፡፡
ዕውቀቶቻችን ሁሉ ለጋራ ጥቅም መዋል የማይችሉ ከሆነ ከንቱ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ግን ማንም ሰው ስለተማረ ስለራሱ ማሰቡን ትቶ ስለሰው ብቻ ያስባል ወይም ማሰብ አለበት ማለቴ እንዳልሆነ አንባቢ ይገንዘብልኝ፡፡ ዕውቀት ሥራ ላይ ዋለ የሚባለው ለሽያጭ ሲቀርብ መሆኑ አይካድም ሽያጩ የንዋይ ልውውጥ ይኑረውም አይኑረውም፡፡ ለሽያጭ ቀረበ ማለት ደግሞ ለሕዝብ ጠቀሜታ እና ዕይታ ዋለ ማለት ነው ስለዚህም በማንኛውም መንገድ ለሕዝብ ጠቀሜታ የዋለ አገልግሎትም ሆነ ቁሳዊ ምርት መና መሆን የለበትም፡፡ ዘመን ተሻጋሪ አስተሳሰብና ተግባር ማራመድ አለብን፡፡ ዛሬ በደመ ነፍስ ተናግረን ነገን መልስ የሌለን ወይም የሚያስወቅሰንን ነገር መፈጸም የለብንም፡፡ ለዚህም ነገን እያሰብን መሥራቱ ተመራጭ እና የአስተዋይት ውጤት ነው፡፡

ሁልጊዜም በጎ በጎውን ማሰብ መልካም ነው ነገ መልካምነታችን ዋጋ ይከፍለናል